የሀገር ውስጥ ዜና

ሕወሃትን የሚያወግዝ ሰልፍና ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ በወላይታ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተካሄደ

By ዮሐንስ ደርበው

July 29, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪውን ሕወሃት እኩይ ተግባር የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍና ለመከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ በወላይታ ዞን ዳሞት ሶሬ ወረዳና በጉኑኖ ከተማ አስተዳደር ተካሄደ።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ተገኝተዋል።

በሰልፉ ላይ የአሸባሪውን ህወሓት ትንኮሳ እናከሽፋለን፣ የጦር መሳሪያ ከትግራይ ሕጻናት ትከሻ ይውረድ፣ ብሔራዊ ጥቅማችንና ሉዓላዊነታችን ይከበር፣ ክብርና ሞገስ ለመላው ፀጥታ ኃይላችን መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡

የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወንድሙ ደጀኔ የስግብግቡን ጁንታ ሴራ ለማክሸፍ ሁሉም በሀገር አንድነት ስሜት መረባረብ አለበት ብለዋል።

ጁንታው ጨቅላ ሕጻናትን ለጦርነት በሐይል መጠቀሙም የቡድኑን ጭካኔ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዳሞት ሶሬ ወረዳ አስተደዳሪ አቶ ሙሉ በርገኔ በበኩላቸው ጁንታው ሀገር ለማፈራረስ እየሰራ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን በማድረግ ዓላማውን ማክሸፍ ይገባዋል ነው ያሉት።

በማቱሣላ ማቴዎስ