የሀገር ውስጥ ዜና

የአሶሳ-ዳለቲ መንገድ ግንባታ አፈፃፀም 52 በመቶ ደረሰ

By Alemayehu Geremew

August 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሶሳ-ዳለቲ መንገድ ግንባታ አፈፃፀም 52 በመቶ ደርሷል፡፡

ፕሮጀክቱ÷ የአፈር ቆረጣና ሙሌት ፣ የድልድይ ፣ የተፋሰስ እና የመንገድ ዳር የትራፊክ ምልክቶች እንዲሁም የስትራክቸር ሥራዎችን አካቶ ነው እየተገነባ ያለው፡፡

መንገዱ 69 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን÷ ከመንግሥት በተመደበ ከ731 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ነው እየተገነባ ያለው፡፡

በአካባቢው ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ÷ መንገዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ከአሶሳ – ኦዳቢልዱ – ዳለቲ ያለውን የትራንስፖርት ፍሰት ለማሳለጥ እና በአካባቢው ያለውን የሰሊጥ ፣ የአትክልት ፣ የተለያዩ አዝዕርቶችና የመአድን ምርት በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ ያስችላል ፡፡

በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር ለፕሮጀክቱ መጓተት እንደተግዳሮት የተጠቀሰ ሲሆን ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ ተቀርፎ ፕሮጀክቱን በተገቢው የጥራት ደረጃ ለማጠናቀቅ በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን ከመንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡