የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ዘመናዊ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድዮች ሊገነቡ ነው

By Meseret Awoke

August 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በከተማዋ ቀላል ባቡር መንገዶች እና የቀለበት መንገድ ዘመናዊ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድይ ለማስገንባት በሂደት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

በድልድዮቹ የግንባታ ዲዛይን እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኤጀንሲው አመራሮች እና የቻይናው ዥ ያንግ ዚ ዘ ሰከንድ ከተባለ የግንባታ ኩባንያ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በከተማዋ በቀላል ባቡር መንገድ የሚጨናነቅባቸው ጉርድ ሾላ፣ መሪ ሲ ኤም ሲ እና ጎጃም በረንዳ እንዲሁም በአዲስ ሰፈር ሃኪም ማሞ በተባሉ አከባቢዎች የሚገነቡት ዘመናዊ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች ግንባታ የሚሆን ጥናት እና ዲዛይን ላይ ነው ውይይት የተደረገው፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ግርማ÷ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት በማቀላል እና የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደርጋል ማለታቸውን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እነዚህ ድልድዮቹ ከዚህ በፊት የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው ሰው የማይጠቀምባቸው አይነት እንዳይሆን ተገቢው ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው÷ አካል ጉዳተኞችንም ባመከለ መልኩ ምቹ እንደሚሰሩ ኢንጂነር ብርሃኑ አመልክተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የቀረበው ጥናት ድልድዮቹ በሚገነቡባቸው ቦታዎች የመሬት አጠቃቀም፣ ወደ መንገዶቹ የሚወስዱ መጋቢ መንገዶች፣ የአውቶቡስ እና የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃዎችን፣ የእግረኞች እንቅስቃሴን እና በአካባቢዎቹ የሚስተዋሉ የትራፊክ ፍሰቶችን መሰረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!