አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ እህልን ማቃጠል፣ ተፈናቅለው በካምፕ በተጠለሉ ህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ላይ የፈጸማቸው የጅምላ ጭፍጨፋዎች በዓለም አቀፍ የሽብር ወንጀል ያስጠይቃሉ ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የገንዳውሃ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ማንሳቱ የአገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ነውም ብለዋል ምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በምዕራብ ጎንደሯ ገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪው አባት አርበኛ አዱኛ መለሰ እንደተናገሩት የፌደራል መንግሥቱ ጥሎት የነበረውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማንሳቱ ህዝብን ከአሸባሪው ህውሃት ጥቃት የሚከላከል ነው።
አሸባሪው የህውሃት ቡድን የሚፈፅመውን በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም ይሁን አሁን በጫካ ውስጥ ሆኖ ንጹሃን ዜጎቹን የመጨፍጨፍ እኩይ ድርጊቱን እንደቀጠለበት ገልጸዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ እህልን ማቃጠል፣ ተፈናቅለው በካምፕ የተጠለሉ ህጻናትን፣ ሴቶችና አዛውንቶችን በጅምላ መጨፍጨፍ ቡድኑን በአለም አቀፍ የሽብር ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህ ቡድን በገሃድ የሚፈጽመውን ወንጀል ወደ ጎን በመተው በተቃራኒው መቆሙ ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑንም ገልጸው ሁሉም ሀገር ወዳድ ህዝብ ይህን አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
“ተጥሎ የነበረውን የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት አድርሷል” ያሉት ነዋሪው አሁን ላይ ውሳኔው በመነሳቱ መንግስት በሚወስደው እርምጃ ከህይወት መስዋዕትነት ጀምሮ ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ባዘዘው አስረሳኝ በበኩላቸዉ ተጥሎ የነበረውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ መሻር አሸባሪው ቡድን በንፁሃን ህዝቦች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር ብለዋል።
“አሁን ላይም መነሳቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ አገር ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነው” ብለዋል።
ይህን ቡድን ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ ለመደምሰስ መንግስት ብቻ ሳይሆን ከመላ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ የህልውና ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን ላለ ቡድን በጋራ ሆኖ መደምሰስ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሊሰጠው አይገባም” ያሉት አቶ ባዘዘው እርሳቸውም ግንባር ድረስ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
“የውሳኔው መሻር ለሀገር ወዳድ ህዝቦች ታላቅ የደስታ ስሜትን የሚፈጥር እና አሸባሪውን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አንድ እርምጃ ነው” ያለው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት እንድሪስ ካሳ ነው።
“ይህ ቡድን የመጀመሪያ ጠላቱ የትግራይ ህዝብ ነው” ህዝቡን ከሌሎች ወንድሞቹ በመነጠል አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል።
ቡድኑ ሲደመሰስ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በበለጠ የትግራይ ህዝብ እፎይታ የሚያገኝ መሆኑን ገልጾ ለዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀቱን ወጣቱ ጠቁሟል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!