አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምቦ ከተማ በሸቀጦች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአምቦ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ሸማቾች በበኩላቸው በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ለመከላከል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በከተማዋ በሸቀጦች ላይ የሚደረግን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ ግብረ ሃይል መቋቋሙን የአምቦ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኩመላ ሂርጳ ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደረገው ቁጥጥር ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ዋጋ የጨመሩ 34 ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶችና ሁለት መጋዘኖች እንዲዘጉ፣ ለ103 ሱቆች ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ ለ245ቱ የምክር አገልግሎት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ከተወሰነለት የስራ ዘርፍ ውጭ ሲነግዱ የተገኙ የ14 ነጋዴዎች መደብሮችም መታሸጋቸውን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ የሸማች ማህበራትን አቅም ለማጠናከር አየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ባለሱቆች የሸቀጦች የዋጋ ዝርዝር በግልፅ ቦታ እንዲለጠፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎችም ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ የተጋነነ ጭማሪ ማድረጋቸው ከስነ-ምግባር ውጭ መሆኑን ነው ለኢዜአ የገለፁት።
አንድ ኪሎ ስኳር ከሁለት ሳምንት በፊት በ45 ብር ይገዙ የነበረ ሲሆን÷ ሰሞኑን 72 ብር እየተጠየቁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!