የሀገር ውስጥ ዜና

የኮቪድ 19 ህሙማን ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

August 18, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ወራት ከነበረው የኮቪድ 19 ህሙማን ቁጥር አንጻር አሁን ላይ ቁጥሩ በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል የስራ ሀላፊዎች ገለጹ፡፡

በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ህክምና ማእከል ኃላፊ ዶክተር ውለታው ጫኔ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአሁኑ ጊዜ የጽኑ ህሙማን ክፍል ሞልቷል ብለዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት ከነበረው አንጻርም በአስር እጥፍ መጨመሩን ነው የተናገሩት፡፡

በኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ናትናኤል በክረጺዮን ከግንቦት እስከ ሀምሌ የነበረው ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ገልፀው÷ አሁን ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ የህሙማን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በአንድ ጊዜ እስከ 30 የሚደርሱ በጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው÷ የኦክስጅን እጥረትም አልፎ አልፎ እየገጠማቸው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲም በበኩሉ አሁን ላይ የእጅ ጓንት እጥረት መኖሩን ጠቅስው÷ ለኮቪድ 19 ህክምና የሚያገለግሉ ግብዓት እጥረት እንዳይገጥም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተወሰኑ ቦታ ብቻ የሚሰጠውን አገልግሎት በ180 በሚደርሱ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ህክምናውን ለማዳረስ እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በሲሳይ ጌትነት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!