ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ በአፍጋኒስታን እንድትቆይ በአጋሮቿ ጫና እየተደረገባት ነው

By Alemayehu Geremew

August 24, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዳይወጣ በአጋር ሀገራት ግፊት እየተደረገበት መሆኑ ተነገረ፡፡

ግፊቱ ሀገሪቷን ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ ለመስጠት እንደሆነም ነው የተሰማው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአፍጋኒስታን 5 ሺህ 800 የአሜሪካ ወታደሮች ይገኛሉ ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

አሜሪካ የወታደሮቿን ቆይታ ለማራዘምም በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ውሳኔ እንደምታሳልፍ ይጠበቃል፡፡

ከአንድ ሣምንት በኋላ ለቀው እንዲወጡ ጊዜ የተቆረጠላቸው የአሜሪካ ወታደሮች የካቡል አየር መንገድን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ለማወቅም ተችሏል፡፡

ታሊባኖች ከአሜሪካ ጋር በተስማማነው መሰረት ከተቀመጠው ቀነ-ገደብ ውጪ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም የውጪ ኃይል ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ተጠያቂ አይደለንም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

አሜሪካ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 14 ጀምሮ 48 ሺህ ያህል ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷ ነው የተገለፀው፡፡

ሌሎች ከሀገሪቷ መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች በዋና ከተማዋ ካቡል በሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጨናንቀው ተራቸውን እየጠበቁ እንደሆነም መረጃዎች ያመላክታሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚመራው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት በጉዳዩ ላይ ለመምከር ዛሬ እንደሚገናኙ ይጠበቃል፡፡

በርካታ በሀገሪቷ የሚገኙ ከውጭ ኃይሎች ጋር ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች በታሊባኖች የሚወሰድባቸውን የበቀል እርምጃ በመፍራት እየኖሩ እንደሆነ ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!