የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን – ተሰናባች ወታደሮች

By Meseret Awoke

August 25, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በዳውሮ ዞን የሚገኙ ተሰናባች ወታደሮችና የፀጥታ አካላት ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የሚገኙ ወታደሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

ተሰናባች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የዞኑ ፖሊስ አባላት እና ሌሎች የፀጥታ አካላት የሽብርተኞችን ሴራ የሚያወግዝና ሀገሪቷን ለመታደግ መዘጋጀታቸውን የሚገልጽ የድጋፍ ሰልፍ በታርጫ ከተማ አካሂደዋል።

በሠልፉም ሺህ መሰናክሎች አያቆሙንም ሺህ ድሎች አያኩራሩንም፤ መርጠናል፤ ተክለናል፤ ሞልተናል፤ ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የብልጽግና ጉዞ በሽብርተኞች አይደናቀፍም የሚሉና መሰል መፈክሮችን ሰልፈኞቹ አንግበዋል።

ሁሉም ሰው በሠላም የሚኖረው ሀገር ሠላም ስትሆን በመሆኑ ዳር ድንበሯን ለመጠበቅና አስፈላጊውንም ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በሠልፉ የተገኙ ወታደሮች መናገራቸውን የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘግቧል።

የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተፈሪ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር÷ ሀገርን መዝረፍ የለመደው የጁንታው ቡድን የክፋት ጊዜው ስላበቃ አሁንም በእልቂት ለማተራመስ ከውጪ ጠላት ጋር በማበር ቢቃጣም ሴራውን ለማክሸፍ ሁሉም ወታደር ከሞራል ድጋፍ ባለፈ ዳግም በግንባር ለመፋለምም ዝግጁ ነው ብለዋል።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በቻሉትና ባላቸው የዜግነት ግዴታ ጎን ለጎን ይህ ሽብር ቡድን ሰርጎ በመግባት የህዝብን ሠላም እንዳይነሳም ለመቆጣጠር የዞኑ ፖሊስ በሙሉ ዝግጅት ማድረጉን የዳውሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር በዛብህ ገዝሙ አመላክተዋል።

በሠልፉ የተገኙት የዳውሮ ዞን ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግስቱ መኩሪያ ከመከላከያ ጉን ሀገርን ለመታደግ የተሠለፉ ወታደሮችን አመስግነዋል፡፡

በተጨማሪም ክብሯንና ገናናነቷን ጠብቃ ለዓለም ተምሳሌ የሆነችውን ሀገር ለነገ ትውልድም ከነክብሯ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ አሸባሪዎችን ለማጥፋት በቻለው ሁሉ ሊያግዝ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!