ዓለምአቀፋዊ ዜና

አረብ ሊግ በአልጄሪያና በሞሮኮ የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ

By Alemayehu Geremew

August 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ አረብ ሊግ እና ሳዑዲ አረቢያ አልጀሪያ እና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ማክሰኞ ዕለት አልጄሪያ ከሞሮኮ በኩል “መተናኮል” መኖሩን በመጥቀስ ከሞሮኮ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች።

ሃገራቱ በአካባቢው ካላቸው ተቀናቃኝነት አንጻርም ላለፉት ወራት ውስጥ መቆየታቸው ይነገራል።

ይህን ተከትሎም የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ ለአካባቢው ፀጥታና መረጋጋት ሲባል ሁለቱ ሀገራት ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲወያዩ ጥሪ አቅርባለች፡፡

የአረብ ሊግ ዋና ፀሃፊ አሕመድ አቡል ጌይት በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ፍላጎታቸውን በመገደብ የበለጠ ቀውስ እንዳይከሰት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

አልጄሪያን የምታዋስናት ሊቢያም ሁኔታው በጣም አሳዛኝና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያበላሽ እንደሆነ ገልፃ ድርጊታቸውን እንዲያጤኑት ጥሪ አቅርባለች።

አሁን የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከሰተው አለመግባባት የተፈጠረው በምእራብ ሰሃራ በተፈጠረው ችግር እንደሆነ ጠቁመው የግንኙነታቸው መሻከር ግን ይበልጥ የተባባሰው ባለፈው ሳምንት በአልጄሪያ በተከሰተው ሰደድ እሳት ሞሮኮ የአልጄሪያ እጅ አለበት ብላ ጣቷን ከቀሰረች ወዲህ ነው ተብሏል፡፡

ሊቢያ ከመስከረም 7 እስከ 9 በምታስተናግደው የአረብ ሊግ ጉባኤ ቀጠናዊ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቧን የአልጀዚራ ዘገባ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን