የሀገር ውስጥ ዜና

በሠርጉ ዕለት ለተፈናቀሉ ወገኖች ገንዘብ ያሰባሰበው ሙሽራ

By Meseret Awoke

August 26, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ሙሽራው በሠርጉ ዕለት ከራሱ በተጨማሪ ታዳሚዎቹን በማስተባበር ከ395ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል አሰባሰበ፡፡

ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው የአፋር ክልል ተወላጁ ወጣት ሁሴን አህመድ ባለፈው እሁድ ነው በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የተሞሸረው።

በዕለቱም ደስታውን ሙሉ ይሆን ዘንድ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ በግፍ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖቹ የሚችለውን ያህል ድጋፍ ለማድረግ በውስጡ ሲመላለስ የነበረ ሃሳብ መድረክ ላይ ወጥቶ ያቀርባል።

በዚህም እንደመነሻ እሱ 30ሺህ ብር በማዋጣት ሁሉም የሚችለውን እንዲረዳም በመድረኩ ላይ ለታዳሚው ጥያቄ አቀረበ።

ይህን ተከትሎ በሰርጉ ፕሮግራም የታደሙ ወዳጆቹና ሚዜዎቹ የሙሽራውን ሃሳብና ጥያቄ በሙሉ ድምጽ በመቀበል ባደረጉት የገቢ ማሰባሰብ ስነ-ስርዓት 395ሺብር ማግኘት እንደቻለ ነው ሙሽራው ወጣት ሁሴን አህመድ ለኢዜአ የተናገረው።

በዚህም መደሰቱንና አስተዋጽኦ ላደረጉ ወዳጆቹ ምስጋናውን አቅርቧል።

በአሜሪካና ሌሎች ሀገራት የሚገኙ ጓደኞቹም ሃሳቡን በመቀበል ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳታቸውን ጠቅሶ÷ ወደ አሜሪካ ሲመለስም ዲያስፖራውን በማስተባበር ድጋፉን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የተሰበሰበው ገንዘብም ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ በተቋቋመው ኮሚቴ ስም በተከፈተው የሂሳብ ቁጥር በቅርብ ቀን ገቢ ይሆናል ብለዋል።

በክልሉ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና የሰብአዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተቋቋመው ኮሚቴ አባል አቶ ሰዲቅ በድሩ በበኩላቸው÷ ወጣቱ በሠርጉ ዕለት ለተጎጂ ወገኖቹ ያደረገው ድጋፍ የሚደነቅና ለሌሎችም አርአያ ሊሆን የሚችል በጎ ተግባር ነው ብለዋል።

ይህም አንድ ሆነን እርስ በራሳችን ከተረዳዳን አሸባሪው ቡድን የደቀነብንን የህልውና አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ መቀልበስ እንደምንችል የሚያሳይ በመሆኑ ሌሎቹም መሰል የሰብአዊነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!