አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ከክልሉ ከሁሉም ወረዳዎች ከተወጣጡ መምህራን ጋር በጅግጅጋ ከተማ ተወያዩ።
በመምህራን መኖሪያ ቤት፣ በመሬት፣ በጥቅማጥቅም፣ የደሞዝ ጭማሪና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ከለውጡ በኋላ በክልሉ የሰፈነው ሰላምና ፀጥታ በሰላም በመንቀሳቀስ ስራቸውን እንዲያከናውኑ እንደረዳቸውና ከለውጡ በፊት ፍርሃት በተሞላበት ሁኔታ ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
መምህራን ያለባቸውን መሠራታዊ ችግሮች በተለይ የቤት ችግርና ጥቅማጥቅም እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት የመምህራን አቅም የማሳደግና የኑሮ ሁኔታቸውን ለማስተካከል የክልሉ መንግሥት ሰፊ ስራዎችን መስራቱን የገለፁት የሶማሌ ክልል ትምሀርት ቢሮ ሀላፊ አቶ መሀመድ ፋታህ፣ የመምህራን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመቅረፍ ባለፉት ሶስት አመታት የክልሉ መንግሥት ከገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል 25 በመቶ ለመምህራን መሰጠታቸው ተናግረዋል።
መምህራን የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት ከዲፕሎማ እስከ ሶስተኛ ድግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
መምህራን ትውልዶችን የመገንባት ሀላፊነትን ተሸከመው እየሰሩ ስለሆኑ ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ።
የክልሉ መንግሥት የመምህራን አቅምና ኑሮ ለማሻሻል ደረጃ በደረጃ እየሰራ ነው ማለታቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መምህራን ያላቸውን ልምድና እውቀት ወደ መንግሥት መዋቅር ገብተው እንዲሰሩ የክልሉ መንግሥት ያደርጋል ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!