አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዱባይ ኤክስፖ 2020 ኢትዮጵያ የምድረ ቀደምት እና የዕድሎች ምድር መሆኗን በሚያስገነዝብ ጭብጥ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከኤሜሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ኤክስፖው ኢትዮጵያ የበለፀጉ ቅርሶች እና ዕድሎች እንዳሏት ለማሳየት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ኢንዱስትሪ ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ ፣ የባህል ብዝሃነት እና የተፈጥሮን ሐብት እንደሚያሳዩ ገልፀው÷ በኤክስፖው ላይ የሉሲ ቅሪተ አካል ምስለ ቅርፅ ለ182 ቀናት ለጉብኝት እንደሚቀርብም ነው የታወቀው፡፡
ኢትዮጵያ እስከ 2045 ልትደርስ ያሰበችውን ራዕይ የሚያሳይ መርሃ ግብርም እንደሚኖር የተመላከተ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የሚያጎለበት እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ኤክስፖው ኢትዮጵያ በንግድ ፣ በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመላው ዓለም ላይ የተሻለ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲኖራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬት በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በተለይም በኢኮኖሚ ፣ በኢንቨስትመንት ፣ በንግድ እና በቱሪዝም ዘርፎች የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኗን በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያም ተሳትፎ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚረዳ መናገራቸውን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!