የሀገር ውስጥ ዜና

የሶማሌ ክልል የጋዜጠኞች ማህበር ተመሰረተ

By Tibebu Kebede

September 19, 2021

 

አዲስ አበባ መስከረም 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ዛሬ ተመሰረተ፡፡

የሶማሌ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ በዴል በምስረታ ፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር የማህበሩ መመስረት ለክልሉ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎችም የሚስተዋሉ የመረጃ ጉድለቶችን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መስራት እንደሚጠብቅባቸው አሳስበዋል።

የቢሮ ኃላፊው ÷ በጋዜጠኞችና በመንግሥት መካከል ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖር እና ከክልሉ ጋዜጠኞች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማግኘት እንዲቻል ሁሉም የክልሉ ሚዲያ ባለሙያዎች የተመሰረተውን የሙያ ማህበር መቀላቀል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሚዲያ ምክር ቤት ተወካይ አቶ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ሚዲያ ምክር ቤት፣ ለክልሉ ጋዜጠኞች ማህበር እውቅና በመስጠት በአቅም ግንባታ እና በልምድ ልውውጥ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ።

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ወ/ት አያን ሹክሪ÷ የማህበሩ ምስረታ በርካታ መሰናክሎችን ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማህበሩ ለሁሉም በክልሉ ለሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ክፍት ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!