የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተሸኙ ወንድማማቾች

By Alemayehu Geremew

September 21, 2021

አዲስ አበባ፣መስከረም 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪውን የህወሓት ቡድንና ጀሌዎቹን ለመደምሰስ ከደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች ጋር ሠራዊቱን ከሚቀላቀሉት መካከል የአንድ ቤተሰብ ወንድማማቾች ተገኝተዋል።

ከላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የተሸኘው ተመሥገን ተስፋዬ ከታናሽ ወንድሙ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ቆርጠው እንደተነሱ ነው የተናገረው።

ዘማች ተመሥገን ተስፋዬ÷ አባቴ ወታደር ነበር፤ ስለውትድርና እና ስለ ሀገር ፍቅር እያስተማረኝ ነው ያደኩት፤ ቢሆንም ግን እኔ ጠላት ከተማችን ገብቶ የሠራውን በደልና ግፍ እስካይ ድረስ ወደ ውትድርና ዓለም ለመግባት አስቤ አላውቅም ብሏል።

ጠላትን ድባቅ ለመምታት ከታናሽ ወንድሙ ጋርም እንደተነሱ ነው የገለፀው።

ዘማች ታድሏል ተስፋዬ በበኩሉ÷ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ከልጅነቱ ጀምሮ ውትድርናን ሲመኝ እንደነበረና ከታላቅ ወንድሙ ጋር በመሆን መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀሉ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል።

ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድም ሃገሩን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ወላጅ ቤተሰቦቻቸውም ወንድማማቾቹ የሃገርን ዳር ድንበር እንዲያስከብሩ መርቀው እንደሸኟቸው ነው የገለጹት።

ወንድማማቾቹ÷ አንዳንድ ወጣቶችም ከአጉል ነገሮች ታቅበው የሃገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች በነቂስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉ ሲሆን÷ ወጣቶቹ ዛሬ በደብረ ታቦር ከተማ አሸኛኘት እንደተደረገላቸው አሚኮ ዘግቧል።