የሀገር ውስጥ ዜና

ኢጋድ በኢትዮ- ኬንያ ድንበር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

By Alemayehu Geremew

September 22, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢጋድ በኢትዮ- ኬንያ የጋራ ድንበር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ “ሞያሌ-ሞያሌ” የተሰኘ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ከኢትዮጵያና ኬኒያ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር በመሆን ፕሮጀክቱን በሚመለከት በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።

የኢጋድ የጤናና የማህበራዊ ዘርፍ ዳይሬክተር ፋቲያ አልዋን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢጋድ አባል ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ለማጎልበት የሚያግዙ ሶስት ፕሮጀክቶች ተለይተዋል።

በዚህም በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የ”ሞያሌ-ሞያሌ” ፕሮጀክት፤ በኢትዮጵያና ሱዳን “መተማ ጋላባት” ፕሮጀክት እንዲሁም በኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበር “አሊሰቤ ክልል” ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ለሶስቱ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ምእራፍ ትግበራ ከጀርመን መንግስት በተገኘ 20 ሚሊዮን ዩሮ በጀት መያዙን ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ ለ”ሞያሌ- ሞያሌ” ፕሮጀክት 4 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ገልጸዋል።

“ሞያሌ- ሞያሌ” ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሙከራ ደረጃ የቀጥታ ገንዘብ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፤ በዚህም ከሁለቱም ወገን አንድ ሺህ 600 ቤተሰቦች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በቀጣይ ሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ጌቱ ግርማ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርተዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ጃኒ ኤንድሩ፤ ፕሮጀክቱ በተለይ በሁለቱ ሀገሮች ድንበር ላይ የሚኖሩ ስደተኞችን ጉዳይ ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

ሁለቱ ሀገሮች በሚዋሰኑባቸው ድንበሮች ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ተወካይ ነጋ ሞረዳ ናቸው።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል በኬኒያ ከሚገኘው የመርሳቤት ክልል ጋር እንደሚዋሰን አንስተው፤ በአካባቢው የሚኖሩ ህዝቦች ባህልና ቋንቋን ጭምር የሚጋሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

በኬንያ የማርሳቤት ክልል አስተዳዳሪ ተወካይ አብዱልቃድር ሱሌማን፤ የፕሮጀክቱ ይፋ መሆን በሁለቱ ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች ያላቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የባህል ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ኬኒያ የድንበር አካባቢ ያለውን ትስስር የሚያሳልጥ ቢሮ ሁለቱ ሀገራት በሚዋሰኑባቸው ሞያሌ እንደሚገነባም ኢጋድ አስታውቋል።