የሀገር ውስጥ ዜና

ከመተማ – ጎንደር የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም እንዲቋረጥ በሚሰራ ጠላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል – መምሪያው

By Alemayehu Geremew

September 23, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመተማ – ጎንደር የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም እንዲቋረጥ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም የጠላት ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ አስጠነቀቀ።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሠላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ እንዳለው ማሩ÷ በጽንፈኛው የቅማንት ቡድን ሴራ ምክንያት ለወራት ተዘግቶ የነበረው ከጎንደር – መተማ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን አስታወቁ።

ኃላፊው÷ በመንግሥት ሆደ ሰፊነት መንገዱ ለወራት ሲከፈትና ሲዘጋ እንደነበረ ገልፀው÷ አሁን ላይ ግን ዞኑ መንገዱን ዳግም ለማዘጋት በሚንቀሳቀስና በሚተባበር ማንኛውንም የውስጥ ጠላት ላይ እርምጃ ለመውሰድና ለመደምሰስ አቋም እንደያዘ ነው የተናገሩት፡፡

የመንገዱ መዘጋት በዞኑ ማኅበረሰብ ብቻም ሳይሆን በክልሉና በሀገር ደረጃም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ አስከትሏልም ብለዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም÷ የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን ማዘዣ ጣቢያውን ጭልጋ አድርጎ ሌንጫ፣ ጉባይ፣ ሽንፋና መቃ አካባቢ ሽፍቶችን በማደራጀት ንጹሃን ዜጎችን ሲዘርፍና ሲያግት፣ የልማት አውታሮችን አገልግሎት እንዳይሰጡ ሲያቋርጥ እንደ ነበር ገልጸዋል።

የሽብርተኛው ህወሓት ቡድን ተላላኪና ቅጥረኛ የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን በቲሀ በኩል ሽብርተኛውን አስገብቶ የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ቢሞክርም በዞኑ የጸጥታ ኃይልና ማኀበረሰብ ጀግንነት መደምሰሱን ነው አቶ እንዳለው የገለጹት።

መንገዱን በዘላቂነት ፍጹም ሰላማዊና አስተማማኝ ለማድረግ የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ የምዕራብ ጎንደር ዞንና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

መንገዱ ለኅብረተሰቡ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥም ጽንፈኛ ቡድኑን አሳልፎ እንዲሰጥ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ውይይት መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

ዳግም የዘረፋና እገታ ወንጀል በሚፈጸምበት ቦታ ድርጊቱን እያየ የማያጋልጥ አካል ተጠያቂ እንዲሆንም ውሳኔ መተላለፉን የዘገበው አሚኮ ነው፡፡