አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ለተፈናቃይ ወገኖች 26 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስና ምግብን ያካተተ ነው።
የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ እና የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ድጋፉን ለደሴ ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል።
የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መሥቀል ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ዘርፍ ዴኤታ ሙና አህመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ አሸባሪው ቡድን በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ላይ ያደረሠውና እያደረሠ ያለው ጉዳት አሰቃቂነቱ የከፋ መሆኑን ገልጸዋል።
የህወሓት ችግር የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ብልጽግና ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑን አሁን እያደረገ ያለው ጥፋት ያሣያልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ።
አሸባሪው ቡድን በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ላይ ያደረሠውና እያደረሠ ያለው ጉዳት አሰቃቂነቱ የከፋ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ መላው ኢትዮጵያውያን የደረሠውን ችግር ለመቋቋምና የበለጠ አንድነቷ የተጠበቀና በብልጽግና ፍኖት የምትጓዝ ሀገርን ለመገንባት በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሁላችን መኖሪያ የጋራ ሀብታችን ናትና ሁላችንም ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል በደጀንነት በመሠለፍና ተፈናቃይ ወገኖቻችንን በመደገፍ አለኝታ ልንሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በአለባቸው አባተ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!