የሀገር ውስጥ ዜና

ያሆዴ መስቀላን ስናከብር ከቀያቸው የተፈናቀሉትንና የሃገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ነው

By Meseret Awoke

September 23, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የሀድያ የዘመን መለወጫ “ያሆዴ መስቀላ” በዓል በአባቶች ምርቃት በሆሳዕና ከተማ ተከብሯል።

የዘንድሮው የሀድያ ብሄር የዘመን መለወጫ “ያሆዴ መስቀላ” ሲከበር የዞኑ ህዝብ ለበዓሉ ከሚያወጣው በመቀነስ ከቀያቸው በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉና ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረግ መሆን እንዳለበት የሀድያ የባህል አባቶች አሳስበዋል።

በባህላዊ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሃገር ሽማግሌ ዳኛ ዋሚሾ ሽፈራው እንዳሉት÷ ያሆዴ መስቀላ ዘመን መለወጫ በዓል ዘንድሮ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው እኩይ ተግባር የንጹሀን ህይወት በጠፋበትና በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው በተፈናቀሉበት ሁኔታ በድምቀት አይከበርም።

በዓሉ በምርቃትና በድጋፍ እንዲከበር የባህል አባቶች በወሰኑት መሰረት መላው የሀድያ ህዝብ ለበዓሉ ከሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የብሄሩ አባ ገዳ ዮሀንስ ኤርዱሎ በበኩላቸው÷ “በአሸባሪው ቡድን የሃገር ሰላም በታወከበትና በርካቶች በተፈናቀሉበት ሁኔታ በዓሉን በደመቀ መልኩ ማክበር ለሃገርና ለወገን አለማሰብ ነው” ብለዋል።

በግላቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት አባገዳ ዮሀንስ÷ ሁሉም ከዚህ አንጻር ሀላፊነት እንዳለበት አውቆ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

“በሀገር ላይ የሚደቀኑ አደጋዎችን ለመመከት ሁሌም በአንድነት ስንዘምት ቆይተናል፤ አሁንም የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በጋራ መነሳት አለብን” ያሉት ሌላው አባገዳ አበጋዝ ጊንታሞ ናቸው።

“አሸባሪው ቡድን በራሱ የሚያደርገው አንሶ ለውጪ ጠላቶች አሳልፎ ሊሰጠን እየተራወጠ ነው” ያሉት አባገዳው ቡድኑን በመደምሰስ የሃገር ህልውናን ማስከበር አለብን ብለዋል።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ማቲዮስ ሎምበሶ በበኩላቸው÷ የህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ላሉና ተፈናቅለው ለእንግልት የተዳረጉትን ወገኖች በመደገፍ በዓሉን ማክበር ይገባል ነው ያሉት።

የዞኑ ህብረተሰብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። በሽብር ቡድኑ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀድያ ብሄር በድምቀት የሚከበሩ በዓላት በሃገር ላይ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ በምርቃትና በልገሳ እንዲከበሩ የሚደረግ መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ላይ መነሳቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!