የሀገር ውስጥ ዜና

የአይከል ከተማን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለሰ እየተሰራ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

September 29, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የአይከል ከተማን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለሰ እየተሰራ መሆኑን የአይከል ከተማ ከንቲባ ነገሰ ብርቄ ገለጹ።

በከተማዋ እና በዙሪያዋ ወረዳ ከሚያዝያ 5 2013 ጀምሮ በተፈጠረው የፀጥታ ቸግር ምክንያት ንፁሃን ዜጎች እንዲሞቱ እንዲፈናቀሉና ንብረታቸው እንዲቃጥል አድርጓል።

የከተማ ነዋሪዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት÷ የቅማንት ፅንፈኛ ቡድን በአካባቢው በፈጠረው የፀጥታ ቸግር የኢኮኖሚ አቅማቸው እየተዳከመና በተረጋጋ ሁኔታ ህይወታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ገልፀዋል።

ቡድኑ ንፁሃን ዜጎችን በማገት በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቀዉስ መፍጠሩን የተናገሩት የአይከል ከተማ ነዋሪዎች ይህን ቸግር መንግሥት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

መንገዱ መዘጋቱ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የንግድ ስራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ÷ መንግስት አስተማማኝ የደህንነት ስራ በመስራት መንገዱን እንዲያስከፍትላቸው ጠይቀዋል።

የአይከል ከተማ ከንቲባ አቶ ነገሰ ብርቄ እንደሚሉት÷ በአለመረጋጋት ውስጥ የቆየችውን የአይከል ከተማ ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

ተቋርጦ ለአምስት ወራት የቆየው መደበኛ የመንግስት አገልግሎት ተጀምሯል ያሉት ከንቲባው÷ ባንኮችም አሁን ላይ ወደ ስራ ተመልሰዋል ብለዋል።

በከተማዋ የተፈጠረውን ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት ከፀጥታ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ከንቲባው አመልክተዋል።

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!