የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር  የ9 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ስምምነት ተፈራረመ

By Meseret Demissu

October 01, 2021

አዲስ አበባ መስከረም 21፣ 2014 (ኤፋ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬድዮ ግንባታ ለመገንባት የሚያስችለው የ9 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ውል ተፈራረመ።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠውና የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ዑባህ አደም ፈርመዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ፋና ወጊ መሆኑን የተናገሩት አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ ለድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሚገነባው የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ከግንባታ በዘለለ፣ተቋማቱ በሚዲያ ኢንደስትሪ ዘርፍ በቀጣይነት በትስስር  እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አያይዘውም  ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፥ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ግንባታን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ዑባህ አደም በበኩላቸው፣ የማህበረሰብ ሬድዮ መገንባት ዩኒቨርስቲው በምርምር ያወጣቸውን ስራዎች ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳው ተናግረዋል።

ከአንጋፋው የሚዲያ ድርጅት ጋር በጋራ ስንሰራ ይህ ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው አይደለም ያሉት ፕሬዚደንቷ፥ በቀጣይም ሙያዊ እገዛዎችን በመለዋወጥ ለሁለትዮሽ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

 

የዩኒቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው፥ የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ መገንባት የረዥም ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም የሬድዮ ጣቢያ መገንባት ለዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው አገልግሎት በዘለለ፥ የፋና ፕሮግራሞች ተደራሽ በማይሆኑባቸው ቦታዎች ላይ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በትብብር ለመስራት ያስችላል ብለዋል።

በእዮናዳብ አንዱዓለም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!