አዲስ አበባ፣ መሰከረም 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተለያዩ ደረጃዎች በጋዜጠኝነት ያገለገለው ጋሻው ጫኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ጋዜጠኛ ጋሻው ከአባቱ አቶ ጫኔ ብዙነህ እና እናቱ ወይዘሮ የሽመቤት ታዬ በኦሮሚያ ክልል የቀድሞው ኢሉባቡር ዋና ከተማ መቱ በ1958 ዓ.ም ነው የተወለደው።
ጋዜጠኛ ጋሻው ከ30 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤትና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋዜጠኝነት፣ በአርታኢነትና በሌሎች ተያያዥ የኮሙንኬሽን ሥራዎች አገልግሏል።
በአፍላ ወጣትነት አድሜው በኢዜአ ስራ የጀመረው ጋዜጠኛ ጋሻው በዚሁ ተቋም ለ20 ዓመታት አገልግሏል።
በኢዜአ በመቱና ጋምቤላ ከተሞች በወኪልነተ ከዛም በአዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት ከዜና ሪፖተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነተ ያገለገለ ባለሙያ ነበር።
ጋዜጠኛ ጋሻው በዜና አፃፃፉ የተዋጣለት የነበረ ከመሆኑም በላይ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ሳቢ መጣጥፎቹም በእጅጉ የሚደነቅ እንደነበር በተለይ የኢዜአ የሥራ ባልደረቦቹ ይገልፃሉ።
ከሁሉም ጋር በእጅጉ የሚግባባ እና ጨዋታ አዋቂም ነበር ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ።
ጋዜጠኛ ጋሻው ባጋጠመው ድንገተኛ ህመም በትናንትናው እለት ማረፉን ወንድሙ አቶ ቁምላቸው ጫኔ በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ጋሻው ባለትዳርም ነበር።
የጋሻው ጫኔ የቀብር ሥነ-ሰርዓትም ነገ መስከረም 24 ቀን ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ብሄረ ፅጌ ማሪያም ቤተ-ክረስቲያን ይፈፀማል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።