አዲስ አበባ፣ መሰከረም 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ የአርማጭሆ ወረዳ አንፃራዊ ሰላም ውስጥ እንደሚገኝና ሰላሙን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተናገሩ።
አሸባሪው የህውሃት ቡድን ከፅንፈኛው የቅማንት ኮሚቴ ጋር ጥምረት በመፍጠር በአካባቢው ወረራ ለመፈፀም ያደረገው ጥረት ከንቱ ሁኖ ቀርቷል ነው ያሉት አስተዳዳሪው።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ንጉሴ ማለደ ይህን ያሉት በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ በጠገዴ አርማጭሆና በአካባቢው በጎ አድራጎት ማህበር በተዘጋጀው የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ ላይ ነው።
ፅንፈኛው የቅማንት ቡድን የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር አካባቢውን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፥ ጥረቱ በሰላም ወዳዱ የአካባቢው ማህበረሰብ ከሽፏል ብለዋል አስተዳደሪው።
ቡድኑ ሰዎችን በማገት፣ የሰርቆት ተግባራትን በመፈጸምና የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ባደረገው እንቅስቃሴ በርካታ የጥፋት ተግባራት ማከናወኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፥ የወረዳው ሰላምእንዲጠበቅ በርካታ አካላት ተሳትፎ አድርገዋል ብለዋል።
በህልውና ዘመቻው የላይ አርማጭሆ ማህበረሰብ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን የተናገሩት አቶ ንጉሴ ፥ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ተባብሮ ለኢትዮጵያ ሰላም ይታገላል ብለዋል።
የቅማንትን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማጋጨት የሚሞክረውን ፅንፈኛ ቡድን ጥረት የቅማንት ህዝብ የጠገደ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማህበር በወረዳው ሰላም እንዲፈጠር በህዝብ ለህዝብ ውይይትና በተለያዩ ድጋፎች የጎላ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል።
በውይይቱ ላይ ከጎንደር ጠገዴ፥ ታች አርማጭሆና መሀል አርማጭሆ የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በምናለ አየነው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!