የሀገር ውስጥ ዜና

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መካተታቸውና የነዋሪዎች ዕይታ

By Meseret Awoke

October 07, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መካተታቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ባሻገር ሀገር የጋራ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቀረቡ የ22 የካቢኔ አባላትን ሹመት አጽድቋል።

በምክር ቤቱ ሹመታቸው ከጸደቀው የካቢኔ አባላት መካከል ደግሞ ሶስቱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው።

ኢዜአ የካቢኔ ሹመቱን በሚመለከት በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት÷ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መካተታቸው የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ወይዘሮ ጥሩወርቅ ኃይሌ የካቢኔ አወቃቀሩ አካታች የፖለቲካ አመለካከትን ያንጸባረቀ ነው ይላሉ።

በአንድ የፖለቲካ አመለካከት የታጠረና ሀገር የአንድ ፓርቲ ብቻ ናት የሚለውን አስተሳሰብ የቀየረና ዘመናዊ ፖለቲካን የሚያላምድ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ሂደቱ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከማፋጠን አኳያ በጎ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

አቶ አደራዬ አየለ በበኩላቸው÷ የምክር ቤቱ ስብሰባ ብዝሃ አተያይ የጎላበትና የሃሳብ ነጻነት የነገሰበት መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።

የካቢኔ ምልመላው ከፖለቲካ አመለካከት ይልቅ ለትምህርት ዝግጅትና ስራ ልምድ ቅድሚያ መስጠቱ ሹመቱን ፍትሃዊ እንዳደረገውም ነው ያነሱት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አወል አሊ÷ “6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በምርጫው ወቅት ብቻ ሳይሆን በውጤቱም ስኬታማ መሆኑ በካቢኔ ሹመት ማየት ተችሏል” ብለዋል።

ይህም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ምክር ቤት ውስጥ ካገኙት ወንበር በተጨማሪ በመንግስት ካቢኔ ውስጥ መካተታቸው በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ባህል እየዳበረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገር ጉዳይ ላይ መገፋፋት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያሉት ደግሞ አቶ ቦጋለ ቸርነት ናቸው።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት እንዲሁም ሁሉም ዜጋ የሚለፋው ለአንዲት ኢትዮጵያ መሆኑን አንስተው÷ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልልም የታየው ጅማሮ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የቀረበውን ሹመት ማጽደቁ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!