የሀገር ውስጥ ዜና

የህዳሴ ግድብ የሚያመጣቸውን ዕድሎች ወደ ጥቅም ለመለወጥ እንሰራለን – የዳያስፖራ አባላት

By Meseret Awoke

October 12, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚፈጠሩ ዕድሎችን ወደ ጥቅም ለመለወጥ በቱሪዝም መዳረሻ ኢንቨስትመንት ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ።

ከሰሞኑ በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድጋፍ የሕዳሴ ግድቡን የጎበኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ልዑክ በግድቡ ዙሪያ ገባ በጉባ ሰማይ ስር ስላሉ የነገዎቹን የቱሪስት መዳረሻ ዕድሎችን ቃኝቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የልዑኩ አባላት እስካሁን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብም ሆነ በሌሎች ተሳትፎዎች ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ቴክሳስ ነዋሪ የሆኑት የቀድሞ ፖሊስ ሠራዊት አባል መቶ አለቃ ንጉሴ ሲገኝ ከኢትዮጵያ ከተሰደዱ 41 ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ዓባይ ለአገር ብልጽግና ሊውል መቃረቡን ተመልክተው መደሰታቸውን ይገልጻሉ።

ግብጽና ሱዳን በዓባይ ወንዝ ለዘመናት በብቸኝነት ሲጠቀሙበት መኖራቸውን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓባይ ውሃ ለመጠቀም ወደሚጨበጥ ተስፋ ተሸጋግራች ነው ያሉት።

ለግድቡ ስኬት ከሶስት ዓመታት በፊት በተጀመረው በቀን አንድ ዶላር ገቢ በሚደረግበት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ መቶ አለቃ ንጉሴም በዓመት 365 ዶላር በመዋጣት አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በአገር ቤት ከመቀነታቸው እየፈቱ የሚከፍሉ ኢትዮጵያውያን እናቶች እንዳሉ ሁሉ፥ ዳያስፖራው ደግሞ አነስተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ ቢለግስ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የለንደን ነዋሪው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ በበኩሉ፥ ዳያስፖራው በየሙያው ኢትዮጵያን ማገዝ ስላለበት በተለይ የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች የሚፈጥሩትን ውዥንብር የማጥራት ስራ መሰራቱን ገልጾ፥ አሁንም ሰፊ መሰራት እንደለበት ጠቁሟል።

ግድቡን በአካል ከተመለከተ በኋላ በዓባይ ጉዳይ በሙያው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጠው።

የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላቱ ግድቡ ለፍጻሜ እስኪበቃ ከሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ባሻገር ግንባታው ሲጠናቀቅ በሚፈጠሩ የቱሪዝም መዳረሻ ኢንቨስትመንቶች አሻራቸውን እንደሚያሳርፉም አረጋገጠዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባልና የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪው አቶ አለማየሁ ስለሺ፥ ግድቡ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር በቱሪዝም መዳረሻነት ሌሎች ጸጋዎቸን ይዞ ይመጣል ይላሉ።

ሰው ሰራሽ ሐይቁ የሚፈጥራቸውን የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች ማልማትና ለአካባቢው ነዋሪ የስራ ዕድል መፍጠር በተለይም ብዙ ልምድና ሐብት ካካበተው የዳያስፖራው ማህበረሰብ ትልቅ ሃላፊነት ይጠበቃል ብለዋል።

ከ21 ዓመታት በኋላ ከካሊፎሪኒያ ወደ እናት አገራቸው የተመለሱት አቶ ሙሉጌታ ምህረትም፥ ግድቡ ሲጠናቀቅ ለስፖርት መዝናኛነትና ለቱሪስት መዳረሻነት ፋይዳው ጉልህ በመሆኑ አሁንም ቀጣይንት ያለው ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከሜሪላንድ የመጡት ሲስተር ማርታ ገብረስላሴ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያውያን የነገ ተስፋ ከግድቡ ጀርባ መሆኑን ገልጸው፤ ግድቡን በአካል በማየታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።

የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚመጡ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድሎች በሌሎች አገራት እንደሚታዩት ትልቅ አቅም እንዳላቸውና በዚህ ረገድ የግድቡን መልከ ብዙ ፋይዳ ተረድቶ ዳያስፖራው በሁሉም መስክ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!