የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ምዕራባውያን የከፈቱባትን ጦርነት ድል እንደምታደርግ አምናለሁ – ዶክተር ሙምቢ ሴራኪ

By Alemayehu Geremew

November 17, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶቿን ዳግም ድል እንደምታደርግ አምናለሁ ስትል ኬንያዊቷ የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅ ዶክተር ሙምቢ ሴራኪ ገለፀች።

በተለያዩ የቴሌቪዥን ሾው ዝግጅቶቿ የምትታወቀው ዶክተር ሙምቢ ሴራኪ፥ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያሳዩት ያለውን ጣልቃ ገብነት እና ያልተገባ ጫና በምታዘጋጀቸው ፕሮግራሞቿ አጥብቃ ትኮንናለች።

በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለቴሌቪዥን ተከታታዮቿ ባቀረበችው ዝግጅት ኢትዮጵያ ለብቻዋ ከምዕራባውያን ኃይሎች ጋር ጦርነት ላይ እንደሆነች እና ድል እንደምታደርግ ያላትን እምነት ገልጻለች፡፡

“ሊቢያ ላይ ወረራ የፈጸመው “የኦባማ ቲም” ከጆ ባይደን ጋር ነጩ ቤተ መንግስት ገብቷል” ያለችው ዶክተር ሴራኪ፥ “ይሄ ትግል በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የተከፈተ ዘመቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን ኢላማ ያደረገ ነው” በማለት ተናግራለች።

የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችም በኢትዮጵያ ላይ በርካታ አሉባልታዎችን በመንዛትና የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ላይ መጠመዳቸውን የሲ ኤን ኤን እና መሰል ሚዲያ ተቋማትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስታወስ ትገልጻለች።

ዶክተር ሙምቢ ሴራኪ አፍሪካውያን እንዲነቁና ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጠይቃለች፡፡

ዶክተር ሴራኪ÷ ኢትዮጵያ ከተጋፈጠችው የውጭ ኃይል ጀርባ የግብጽ እጅ አለበት ብላ እንደምታምንም ገልጻለች።

ግብጽ አሜሪካን የመሰሉ አገራትን ሳይቀር ከጎኗ ይዛ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ሲሳናት፥ አሸባሪዎችን አስታጥቃ ቀጠናው እንዳይረጋጋ እየሰራች መሆኑን አስታውቃለች።

ይሁን እንጂ ይህ ሴራ እንደማይሳካና ኢትዮጵያ ዳግም ድል እንደምታደርግ አምናለሁ ብላለች።

ዶክተር ሙምቢ ለአፍሪካውያን ባስተላለፈችው መልዕክት፥ እንደ ሲ ኤን ኤን ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሰራጩትን ሀሰተኛ ዘገባ በማጋለጥና ትክክለኛ መረጃዎችን በማጋራት ኢትዮጵያን እናግዛት ስትል ጥሪ ማቅረቧን ከማኅበራዊ ትስስር ገጿ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም አፍሪካውያን መሪዎች ከገቡበት ሰመመን መቼ እንደሚነቁ አይገባኝም የምትለው ዶክተር ሙምቢ፥ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን የመቆም ግዴታ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች።