የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ክልል የሴቶች አደረጃጀት ከ560 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ አዘጋጅቷል

By Meseret Demissu

November 18, 2021

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 9 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሴት አደረጃጀቶች በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት 21 ድረስ ከ560 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የስንቅ ዝግጅት ማቅረባቸውን  ገለጹ፡፡

የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ እና በድል ለማጠናቀቅም ሁሉም የተጠናከረ ድጋፉን መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሽብርተኛው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉን የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና በህልውና ዘመቻው የሀብት ማሰባሰብና የስንቅ ዝግጅት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ተናግረዋል፡፡

በጋይንትና በደባርቅ አካባቢዎች በርካታ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸውም ኃላፊዋ ለአብነት አንስተዋል፡፡

አሸባሪው  ወራሪ ኃይል ተዘርዝረው የማያልቁ ግፎችን በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ መፈጸሙንም ወይዘሮ አስናቁ ገልጸዋል።

አሸባሪው  ወራሪ ኃይል የፈጸማቸውን ግፎች ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እንዳለ ሁኖ፥ ከችግሩ ለመውጣት አማራጩ ጦርነቱን በአጭሩ እና በድል እንዲቋጭ ለማድረግ በትጋት መስራት ነው ብለዋል፡፡

ክልሉ ለሦስተኛ ጊዜ ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ በርካታ ዘማቾች ወደ ግንባር መዝመታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊዋ በክልሉ የሴቶች አደረጃጀት አስተባባሪነት ከማኅበረሰቡ፣ ከመንግሥትና ከባለሃብቱ ህልውና ዘመቻውን ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ በመደገፍ ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች እንደሆነ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት አስከ ጥቅምት 21/2014 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ560 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የስንቅ ዝግጅት መቅረቡንና ከጥቅምት  ጀምሮ ደግሞ 34 ሺህ 400 ኩንታል ደረቅ ስንቅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ብልጽግና ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መሰሉ ብርሃኑ በበኩላቸው፥  የሴቶች አደረጃጀት የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ ረገድ ያላሰለሰ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ስንቅ ከማቅረብ ባለፈ የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍና ተፈናቃይ ወገኖችን በመርዳት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ትብለጥ መንገሻ እንዳሉት፥  አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል በአጭር ጊዜ መደምሰስ እንዲቻል ሴቶች የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ፡፡

ከስንቅ ማዘጋጀት ባለፈ በጦር ግንባር ተሰልፈው ጀብዱ እየፈጸሙ ያሉ ጀግኖች ሴቶች መኖራቸውን ሊቀመንበሯ ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኃይል እስኪደመሰስ ድረስ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!