የሀገር ውስጥ ዜና

የህልውና ጦርነቱን መሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሠራ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Meseret Awoke

November 22, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህልውና ጦርነቱን መሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ለመገንባት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ÷ የህልውና ጦርነቱን መሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ከመገንባት ጎን ለጎን የዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራም መንግሥት በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ገልጸዋል።

የህልውና ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በተለያየ መልኩ ለመቀነስ ከወዲሁ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ባለፉት አራት ወራት 169 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው÷ ከ157 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን አስረድተዋል።

አፈጻጸሙም 92 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ30 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የአሜሪካ መንግሥት ከአጎዋ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ላይ በያዘው አቋም፥ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን ለአምራች ዘርፉ ለመፈለግ መታቀዱንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

አዳዲስ የገበያ አማራጮችን ከመፈለግ ጎን ለጎን÷ የኢንዱስትሪዎችን የመወዳደር አቅም ለማሳደግ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ነው ተብሏል፡፡

ሌሎች የገበያ ዕድሎችን ለመመልከት ጥናቶች እየተሰሩ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ አንስተው ጥናቶቹም ወደ ኤስያ ሀገራት ምርት መላክ የሚቻልበትን ሁኔታ አማራጭ እየተፈለገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ወደ ህንድ፣ ቻይና እንዲሁም ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ቱርክ ሀገራት በስፋት ምርቶችን ለመላክ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል እስካሁን በስፋት ያልተጠቀምንባቸው የአፍሪካ እና አካባቢያዊ አህጉራዊ ዕድሎች አሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ እነዚህን በስፋት ለመጠቀም መታሰቡን ገልፀዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ያሉበት አካባቢን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተም መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!