አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህውሓት ቡድን በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እየፈፀመ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምናና ተሀድሶ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አበበ ተምትሜ ገለጹ።
አሸባሪ ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ የጥፋት ጥቃቱን ወደ ደም ባንኮች ማዞሩን ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን ፥ የሽብር ቡድኑ ባደረሰው ጉዳትም አራት የደም ባንኮች አገልግሎት አቁመዋል ብለዋል።
ጥቃት የደረሰባቸውም የደሴ ፣የወልዲያ፣ የሰቆጣና የከሚሴ የደም ባንኮች እንደሆኑና ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸው ነው የተመላከተው።
በአሁኑ ጊዜም ከደም ባንኮች መሰብሰብ የነበረበት ከ20 እስከ 25 በመቶ ዩኒት ደም በጥቃቱ ምክንያት ሳይሰበሰብ እንደቀረና ደም ፈላጊ ወገኖች አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው ለከፋ አደጋ ብሎም ሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
የወልዲያ ደም ባንክ አምቡላንስ በሽብር ቡድኑ ተዘርፏል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በሌሎች ደም ባንኮች ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈፀም እንደሚችል ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል።
ለህልውና ዘመቻው ከአራቱ ደም ባንኮች መሰብሰብ የነበረበትን ዩኒት ደም በተሻለ መልኩ ለመሰብሰብ እና ለማካካስ በስድስቱ የደም ባንኮች በትኩረት እየተሰራ ነውም ተብሏል።
በምናለ አየነው