የሀገር ውስጥ ዜና

ላሊበላና ኮምቦልቻ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የጠየቀ ዓለም አቀፍ ተቋም የለም – የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

By Alemayehu Geremew

November 23, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ወደላሊበላ እና ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፍቃድ ቢሰጥም እስካሁን ድረስ ድጋፍ ለማድረስ የጠየቀ አንድም ዓለም አቀፍ ተቋም የለም ሲሉ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ አስታወቁ።

ኮሚሽነሩ ÷ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በአማራ ክልል የሚገኙትን የላሊበላ እና ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያዎች መጠቀም እንደሚችሉ ቢገለፅላቸውም እስካሁን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ የጠየቀ አካል የለም ብለዋል።

በአካባቢዎቹ ለአምስት ወራት ድጋፍ ያላገኙና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች እስካሁን በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ አላገኙም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት በሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለወራት እርዳታ ሳይቀርብላቸው የቆዩ ከአራት ሚሊየን በላይ ዜጎች እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ወደአካባቢዎቹ እርዳታ ጭነው ቢሄዱ እና ሰብአዊ ድጋፍ ቢያቀርቡ ከአምስት ሚሊየን በላይ ዜጎችን መታደግ የሚቻልበት አማራጭ አለ ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።