አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ላደረጉ የአፍሪካ፣ የእስያና ፓስፊክ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ተደረገ፡፡
በዉይይት መድረኩ የከተማዋን የሠላምና የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ ÷ የከተማዋን ሠላም እና መረጋጋት ለማስቀጠል የከተማው የፀጥታ ኃይል ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ከሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል ፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ እና ከሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶች እና ህዝባዊ ሠራዊት የአካባቢያቸውን ሠላምና ፀጥታ የሚያስከብሩ አደረጃጀቶች እስከ ታችኛው የብሎክ መዋቅር ድረስ በማደራጀት ወደ ስራ መግባታቸውን የገለጹት ዶ/ር ቀነዓ አዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በአስተማማኝ ሰላም ላይ መሆኗን አንስተዋል።
በምዕራባዊያን ሚዲያዎች የሚነዙትን የፕሮፖጋንዳ እና የሽብር ወሬ መሬት ላይ ካለዉ የከተማዋ የተረጋጋ ሠላም ጋር ፍፁም የሚጋጭ በመሆኑ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባው የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገልጸውላቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣የኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ÷ በቀጣይ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ከተማ ካደረጉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መሰል ወይይቶች ፤ የግንኙነት መድረኮችን በመፍጠር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በሁለንተናዊ መልኩ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ህዝባዊ የፀጥታ አደረጃጀቶችን በማሰልጠን በሁሉም ወረዳዎች በማሰማራት እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ዙሪያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ሰፊ ማብራሪያ እና ገለፃ በመስጠት የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው መደረጉን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬተሪ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!