የሀገር ውስጥ ዜና

አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው ለፓን አፍሪካኒዝም ዳግም ውልደት በር የሚከፍት ነው – ምሁራን

By Meseret Awoke

November 24, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን ‘ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው የአፍሪካን ጦርነት ነው!’ በሚል ከጎኗ መቆማቸው ለፓን አፍሪካኒዝም ዳግም ውልደት በር የሚከፍት እንደሆነ ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኑ ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ህዝቦች ያቀረቡት ጥሪ ወቅቱን የጠበቀ የተገባ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ÷ በተለይም ድህረ ለውጥ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን የሚል ጠንካራ መንግስት መመስረቱ፣ ከህዳሴ ግድብ ድርድር እስከ ምርጫ የተሄደበትን መንገድ፣ ተላላኪ መንግስት የመመስረት የምዕራባውያን ፍላጎት መጨንገፉ ÷ ምዕራባዊያን በአፍሪካ ሰማይ ስር ማየት ከሚፈልጉት መቃረኑ የውክልና ጦርነት እንዲከፍቱ ማድረጉን ያነሳሉ፡፡

የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ብርሃኑ ሌንጅሶ በበኩላቸው÷ ‘ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው’ በሚል የሚነሳው የአፍሪካዊነት አቀንቃኞች ሀሳብ እውነታውን የገለጠ መሆኑን ያክላሉ፡፡

ዶክተር ብርሃኑ ኢትዮጵያ ማሸነፏ የአፍሪካና የጥቁር ህዝቦች ማሸነፍ ሆኖ እንደሚቆጠር ያነሳሉ፡፡

ይህም ምዕራባውያን ከሚሄዱበት የእጅ አዙር መንገድ የሚገታ ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ የይቻላል ስነልቦና የሚገነባ ድል የሚያደርገው ነው፡፡

በዚህ መሃል ግን የአሜሪካና አጋሮቿ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ይነሳል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን እድል በፈተናዎች ውስጥ እንደሚወለድ አንስተው ÷ ይህ ወቅት ለፓን አፍሪካኒዝም መወለድ እንደመልካም አጋጣሚ ይቆጠራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መነካት በቃ ሲሉ ድምፃቸውን ያሰሙትን አፍሪካውያንና ሌሎችን በማስተባበር ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሚና መጫወት ይጠበቅባታል እንደዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ሀሳብ፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!