የሀገር ውስጥ ዜና

የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን መንግስት አይታገስም- አቶ ማሞ ምህረቱ

By Meseret Awoke

November 24, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደገበያ መቅረብ ያለባቸው ምርቶችን በሚደብቁ እና የጥቁር ገበያ ምንዛሬዎችን በማከናወን የኑሮ ውድነትን በሚያመጡ የኢኮኖሚ አሻጥረኞች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡

አማካሪው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ በህገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ በሚያደርጉ ፤ ወደውጭ ተልኮ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ምርትን በሚደብቁ እና መሰል ወንጀሎች የሚሰሩ ህገወጦችን አድኖ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ህዝቡም ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንዲተባበር ጠይቀው መንግስት በዚህ ወቅት ይህን አይነት ወንጀል የሚሰሩ ወንጀለኞችን እንደማይታገስ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ወደ ተለመደው ሁኔታ ለመመለስ እና የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ እና በተለይም በተፈናቃይ ወገኖች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ሲባል በመንግስት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።

የህልውና ዘመቻው ባጠረ ጊዜ እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም ሁሉም ዜጋ ግብር መክፈል፣ ፋብሪካዎችም የማምረት አቅማቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ የህልውና ዘመቻው የሚፈልጋቸውን ምርቶች ማምረት ላይ ማተኮር፣ ግብርና ላይ መጠነሰፊ የምርታማነት ስራዎች መስራት፣ መንግስትም በለውጡ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል እና መሰል ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወቅቱ ትብብር እና የአገር ፍቅር ስሜትን መላበስ የሚጠይቅ ጊዜ በመሆኑ አሸባሪ ቡድኑ እየሰራ ያለውን አገርን የማፍረስ ስራ ለመከላከል ሁሉም የየድርሻውን መወጣት አለበትም ነው ያሉት።

በዚህ የህልውና ዘመቻ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን ወደጎን በመተው በአንድነት በሁሉም መልኩ የአርበኝነት ስራ ቢሰራ መልካም ነው ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰዉ

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!