የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት በዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ማሳወቁ ጥሩ ጅማሮ ነው – ፕሮፌሰር አን ፊዝት ጌራልድ

By Meseret Awoke

November 24, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በቅርቡ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ማሳወቁ ጥሩ የሚባል ጅማሮ መሆኑን የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊዝት-ጌራልድ ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር አን እንዳሉት ÷ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ የጋዜጠኛነት መርህን ብቻ ሳይሆን የተቋማቸውን የአሰራር ፖሊሲ የጣሰ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ ጦርነቱን ለማሸነፍ የተግባቦት እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅሙን ማጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ ለአንድ ወገን ያደሉ፣ ግጭትን የሚያባብሱ እና ኢትዮጵያን የማጠልሸት ግብ ያላቸው ዘገባዎችን እያሰራጩ ነው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረና በተደራጀ የመረጃ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊዝት-ጌራልድ ÷ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጧቸው ዘገባዎች የዚሁ የመረጃ ጦርነት አካል መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ የሚያወጧቸው ዘገባዎች ኃላፊነት የጎደላቸው፣ የመረጃ ስህተት ያለባቸው እና መሬት ላይ ካለው ነበራዊ እውነት የራቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን “ህወሓት አዲስ አበባን ከቧል” ብሎ በሰራው ዘገባ ላይ የተጠቀመው መስሎች ከዚህ ቀደም ትግራይ ውስጥ የተቀረጸ ምስል መሆኑ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡

ይህ የሲ ኤን ኤን ዘገባ የጋዜጠኝነት መርህና ስነ ምግባርን የጣሰ ከመሆኑ ባሻገር ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን ነው ፕሮፌሰር አን የገለጹት፡፡

ሲ ኤን ኤን ከዚህ ቀደም “የመንግስት ኃይሎች በጦርነት የሞቱ ሰዎች አስክሬን በተከዜ ወንዝ ውስጥ ጥሏል” ብሎ የሰራው ዘገባም እንዲሁ ከእውነታ የራቀና የመረጃ ግድፈቶች የነበሩት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መንግስት ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ክፍተት እንደነበረበትና አሁን ላይ አቅሙን እያሻሻለ መምጣቱንም አውስተዋል፡፡

አሁን ዓለም ባለችበት የመረጃና የዲጂታል ዘመን በተለይም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ዘገባዎች በፍጥነት ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቁመው ÷ በእነዚህ ዘገባዎች የሚፈጥሯቸውን ክፍተት ወዲያው መሙላት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

መንግስት በቅርቡ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ማሳወቁና ይህም ጥሩ የሚባል ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅም በማጠናከር ከመደበኛ ዲፕሎማሲ ጋር በማቆራኘት የተሻለ አቅም መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

መንግስት ጠንካራ የተግባቦት አቅም ሊኖረው እንደሚገባ የሚያነሱት ፕሮፌሰር አን ÷ ተግባቦቱ አጀንዳ መስጠት የሚችል ፣አዝማሚያዎችን ቀድሞ የሚያይና የሀሳብ ትርክቱ ገዢ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የተግባቦት ባህልን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ በስፋት ማስረጽ እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር አን ያብራሩት፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!