አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) አዋሽ ባንክ በ2020/21 በጀት ዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ፡፡
የአዋሽ ባንክ የባለአክሲዮኖች 26ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በስብሰባውም የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ዲባባ አብደታ ÷ በተጠናቀቀው የ2020/21 በጀት ዓመት አዋሽ ባንክ በሁሉም የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡንና ከግል ባንኮች የመሪነት ሥፍራውን ለተከታታይ ዓመታት ይዞ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
በባንኩም የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ መሠረት እ.ኤ.አ. 2025 መጨረሻ ላይ ከአሥር ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን ያስቀመጠውን ግብ በተሳካ ሁኔታ እያሳካ መሆኑን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ይህንን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው በዓለም አቀፍ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተደቀኑበትን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁሞ ስለሆነ ለዚህ ውጤት ያበቁትን አካላት ማመስገኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በ2020/21 በጀት ዓመት የአዋሽ ባንክ ያልተጣራ ትርፍ ለብድር ከሚያዘው መጠባበቂያና ታክስ በፊት ብር 5ነጥብ 58 ቢሊየን ሲሆን ÷ ከመጠባበቂያ ቅናሽ በኃላ ከታክስ በፊት ግን ብር 4ነጥብ8 ቢሊየን ሆኗል፡፡
ትርፉ ከአምናው አንጻር የ34 በመቶ ወይም የ1ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እድገት ያስመዘገበ ሲሆን ÷ የትርፍ መጠን በአዋሽ ባንክ ታሪክም ይሁን፣ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በተቀማጭ ሂሣብ ዕድገት ረገድ ባንኩ ባሣለፍነው ሂሣብ ዓመት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሣብ መጠን ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 መጨረሻ ላይ የ46 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ብር 108ነጥብ 1 ቢሊየን ሆኗል፡፡
ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠንም የ52ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ በማሣየት 87ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ሆኗል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተከታታይ እድገቶችን እያስመዘገበ የመጣ ሲሆን ÷ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የሂሣብ ዓመትም የ44 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ብር 128ነጥብ 7 ቢሊየን መድረሱን ባንኩ ገልጿል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!