አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሚኖሩ የደባርቅና የዳባት አካባቢ ተወላጆች ከሒዩማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለደባርቅና ለዳባት ሆስፒታሎች 23 ሚሊየን ብር የፈጀ ደረጃውን የጠበቀ አልጋና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ሒዩማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳሙ አንለይ÷ለደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል 50 አልጋዎችን እንዲሁም ለዳባት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል 50 አልጋዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ለሁለቱ ሆስፒታሎች በኢትዮጵያ 23 ሚሊየን ብር የሚገመቱ 100 አልጋዎችን ከፋብሪካ እንደወጣ መረከባቸውን ጠቁመዋል።
ድጋፉ ከዚህ በፊት የዳባትና ደባርቅ ሆስፒታሎችን ሲጎበኙ በቂ የሆነ አልጋና የህክምና ቁሳቁስ አለመሟላቱን ማየታቸው ተከትሎ የተደረገ መሆኑም አብራርተዋል።
በህልውና ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት በቂ አልጋ አይኖርም በሚል በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እንደላኩት አብራርተዋል።
የደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያው አማረ በበኩላቸው፥ የደባርቅ ሆስፒታል ከሒዩማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ጋር በመነጋገር ተቋሙን እንዲጎበኝ አድርጎ ይህ አልጋ እንዲመጣ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የዳባት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ መለሰ በበኩላቸው፥ የዳባት ሆስፒታል ስራ ከጀመረ 6 ወራት የሆነው አዲስ ሆስፒታል መሆኑን በመጥቀስ ፤አሁን ካለው የህልውና ዘመቻ አንጻር መንግሥት ሁሉን ነገር ሊያሟላ እንደማይችል ጠቁመዋል።
በመሆኑም ደረጃው የሚጠይቀውን 50 አልጋዎች በሒዩማን ብሪጅ ኢትዮጵያ አስተባባሪነት እና በደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ጥያቄ ጭምር እንዲሟላ መደረጉን ጠቅሰዋል ።
ወደፊት የላቦራቶሪ እቃዎች ቢሟሉ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሰሜን ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!