Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል በግብርናው ዘርፍ ላይ ባደረሰው ውድመት ላይ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ውድመት ባደረሰባቸው አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ የደረሰውን ኪሳራ ለማካካስ የሚያስችል ስራ ለመሥራት ከአጋር አካላት ጋር ምክክር አደረገ፡፡
በአሸባሪው ቡድን ወረራ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች በሁሉም የግብርና ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ በሚቻልባቸው እንዲሁም ወራሪ ሀይሉ ይዟቸው የነበሩና ነፃ የወጡ አካባቢዎች እንዴት በፍጥነት ወደ ልማት ማስገባት እንደሚቻልና ተቋማቱም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
በምክክር ፕሮግራሙ ላይ አሸባሪው ቡድን በክልሉ በሚገኙ ዞኖች ወረዳዎችና ቀበሌዎች ያደረሰው ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት በጥናት ቀርቧል፡፡
የጥናቱን ውጤት እንደ ውይይት መነሻ ያቀረቡት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶ/ር አልማዝ ጊዜው እንደገለጹት፥ በክልሉ 4 ሚሊየን 925 ሺህ 287 ሄክታር መሬት የሚታረስ ሲሆን፥ 122 ሚሊየን 921 ሺህ 548 ኩንታል በላይ ምርት ይመረታል።
አሸባሪው ወራሪ ሀይል ውድመት ባደረሰባቸው አካባቢዎች 2 ሚሊየን 42 ሺህ 402 ሄክታር መሬት የሚታረስ ሲሆን÷ 41 ሺህ 882 ሺህ 796 ኩንታል በላይ ምርት የሚመረትበት ነበርም ብለዋል፡፡
ይህም ከክልሉ አንጻር በእርሻ ማሳ 41 ነጥብ 4 በመቶ፥ ከምርት አንጻር 34 ነጥብ 1 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሀይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው፥ ይህ ወቅት በጋራ አቅደን እና ተመካክረን የጋራ ጉዳያችን ለሆነው የሀገራችን ህዝብ እና ልማት የምንሰራበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
ወራሪ ሀይሉ በክልላችን ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው በግብርና ዘርፍ ላይ በመሆኑ አጋር አካላት ከመቸውም በበለጠ ትኩረት ሊሰጡት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
በምክክር መድረኩ የተገኙ አጋር አካላት የጋራ ምክክር መርሀ ግብር መፈጠሩን አመስግነው የክልሉ ግብርና ቢሮ ያለፉ ችግሮችን ነቅሶ በመውጣት የተቀናጀ አሰራርን ዘርግቶ ወደ ስራ መግባቱ መልካም ጅምር ነው ብለዋል፡፡
ከወራሪ ሀይሉ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚያስፈልገው ዝርዝር የፍላጎት ጥናት በፍጥነት ሊጠና እና ሊገለጽ እንደሚገባ የጠቆሙት አጋር አካላቱ፥ እኛም የፕሮጀክት ማሻሻያዎችን ለመሥራት ያግዘናል ሲሉ ሀሣብ ሰጥተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ አመልድ፣ የግብርና ተጠሪ ተቋማት፣ የህብረት ስራ ማስፋፊያና ማደራጃ፣ የእንስሳት ሀብት ልማት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲእና ግብርና ምርምር ተቋማትና ሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በአለባቸው አባተ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version