Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ የፊታችን አርብ ይካሄዳል።

ሰልፉ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና በመቃወም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዋሺንግተን ግብረ ሃይል አባል አቶ ከባዱ በላቸው፥ ሰልፉ በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰልፉ መነሻውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አድርጎ የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነው ‘ካፒቶል ሂል’ መድረሻውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉም አመልክተዋል።

ሰልፈኞቹ አሸባሪው ህወሓት እየፈጸማቸው ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶች እና የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያሰራጯቸውን ሃሰተኛ መረጃዎችን እንደሚያወግዙም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሰልፉ ላይ በህልውና ማስከበር ዘመቻው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መቆማቸውን የሚገልጹበት መሆኑንም ነው አቶ ከባዱ ያስረዱት።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እንድታቆም የሚያስገነዝብ ደብዳቤ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አንስቶ እስከ ‘ካፒቶል ሂል’ በሚደረገው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ለአሜሪካ ዜጎች በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችን የያዙ በራሪ ወረቀቶች እንደሚበተኑም አመልክተዋል።

በሰልፉ ላይ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ከባዱ ያብራሩት።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደቀረበላቸውም አመልክተዋል።

ዳያስፖራው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ጨምሮ እያከናወናቸው ባሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተወሰኑ ሴናተሮችና የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ላይ እያሳዩ ያለው አቋም መሻሻል እየታየበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ በተለያዩ አማራጮች የአሜሪካ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደሚቀጥልም አስረድተው ÷ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version