አዲስ አበባ ፣ ህዳር 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የማጥናት ሥራ ነገ እንደሚጀመር የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሀላፊ አቶ አንሙት በለጠ እንደገለፁት በክልሉ ከሚገኙ 10 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የ11 የክልል ተቋማት ባለሙያዎችና ወረራ የተፈፀመባቸው ሰባት ዞኖች ተወካዮች በጥናቱ ይሳተፋሉ።
የጥናቱን ግኝት መሰረት በማድረግ መንግስት በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የሚያቋቁማቸውን እና የሚገነባቸውን መሰረተ ልማቶች የመለየት ስራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።
የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከባለሀብቶች፣ ከልማት ድርጅቶች፣ ከዳያስፖራውና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው፥ ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመርና መልሶ ለማቋቋም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጥናቱ ግኝት የክልሉን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈም አሸባሪው ህወሓት ባጠፋው መጠን ፍርድ እንዲያገኝ እንደሚያግዝም አመላክተዋል።
ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርም ሆነ በዘላቂ መንግድ ችግሩን ለመፍታት ለሚካሄደው ጥናት ህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

