አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንግሥት ለሕዝብና ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ቤተሰቦች በመንከባከብና በማገዝ አደራውን እንደሚቀበል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሸባሪውን የህወሃት ወራሪ ቡድን በጀግንነት ሲፋለሙ በርካታ ጠላትን ጥለው በጀግንነት የተሰዉ አባላትና ቤተሰብን አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለሕዝብና ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ቤተሰቦች በመንከባከብና በማገዝ አደራውን እንደሚቀበል ገልጸዋል፡፡
“አሸባሪው ህወሓት ክልሉን ሲወር ክልላችን መቀበሪያው እንዲሆን ያደረጉት ጀግኖች እልፍ አዕላፍ ናቸው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ “በርካታ ጀግኖችም ከጠላት ጋር ተናንቀው ጀብዱ ሰርተዋል፤ ውድና ክብር መስዋዕትነትም ከፍለዋል” ብለዋል።
“ለሕዝብና ለአገር ክብር ሲል ሞትን ንቆ ፊት ለፊት ገጥሞ ከእነ ልጁ በጀግንነት የክብር መስዋእትነት የከፈለው የሸዋው እሸቴ ሞገስ አንዱ” መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እሸቴ ሞገስ ከበኩር ልጁ ይታገስ እሸቴ ጋር ሆኖ ለሕዝቡና ለአገሩ የከፈለው መስዋእትነትና የሠራው ጀብዱ ብዙ ያስተምረናል፤ እሸቴ ሞገስ ከልጁ ጋር በርካታ ጠላትን ጥሎ በጀግንነት አልፏል ሲሉም አውስተዋል፡፡
እሸቴ ሞገስ በጀግንነት ሲዋጋ የወደቀው የልጁ አስከሬን ጥግ ሆኖ ሲዋጋ፥ እርሱም በክብር እንደሚሰዋ እርግጠኛ ሆኖ፣ እያለቀሰ ሳይሆን ለወገን የአርበኝነት ስንቅ በሚሆን አልበገርባይነት ነው ብለዋል።
እሸቴ ሞገስ በጀግንነት ሲፋለም መስዋዕት እንደሚሆን እርግጠኛ በመሆን ለመንግስት ቤተሰቦቼን አደራ ማለቱንም አስታውሰዋል፡፡
በርካቶች እንደ እሸቴ ሞገስ የክብር መስዋእትነት መክፈላቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፥ በየአካባቢው አስገራሚ አርበኝነት የፈፀሙ በርካታ እሸቴዎች አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ ብለዋል፡፡
“እኛም የጀግኖቻችን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍፁም አንረሳም” ያሉት ዶክተር ይልቃል፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዚህ ዘመቻ እንደ እሸቴ ሞገስ ለህልውናቸው፣ ለሕዝብና ለአገራቸው ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ቤተሰቦች በመንከባከብና በማገዝ አደራውን እንደሚቀበልም አረጋግጠዋል፡፡
ለጀግናው እሸቴ ሞገስ ቤተሰቦች ስለ መፅናናት አንነግራቸውም፤ ሌሎችም በክብር ሲወድቁ ስለመፅናናት አናነሳም፤ እነ እሸቴ ሞገስ ከልጅ ትኩስ አስከሬን ጥግ ሆኖ በሐዘን ሳይሆን በጀግንነት መፋለምን አስተምረውናል! ሲወርድ ሲወራረረድ ስንዘክረው የኖርነውን የአባቶቻችን አርበኝነት በዘመናችን አሳይተውናል ብለዋል።
ለሕዝባችንና ለአገራችን እስከመጨረሻው መስዋዕትነት እንድንፋለም የሰጡንን አደራ ተቀብለን ለሕልውናችን እስከመጨረሻው መስዋዕትነት እንታገላለንም ነው ያሉት።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

