Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የተፈናቀሉ ወገኖችን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚጀመር ኮሚሽኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሽባሪው የትህነግ ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ የአሽባሪው ህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ÷ ወራሪው ቡድን ባደረሰው ጉዳት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም እንዳስታወቁት ÷ አሸባሪው ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልል ባደረገው ወረራ ከሁለት ነጥብ አንድ ሚሊየን በላይ ወገኖች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡

ከሰባት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ ወራሪው የሽብር ቡድን ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጽዋል፡፡

ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዳያስፖራዎች በተጠናከረ መንገድ ተፈናቃዮችን ሲረዱ መቆየታቸውን ያስተወሱት ኮሚሽነሩ ÷ አሁንም ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ስንቅ፣ አልባሳት እና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን መንግሥት ብቻውን መወጣት እንደማይችል እና በርካታ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ያስገነዘቡት ኮሚሽነሩ ÷ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ማኅበረሰቡ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል፡፡

በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖች እስኪቋቋሙ ድረስም ከአሁን በፊት ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚሽነር ዘላለም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በርካታ ሥራዎች እና ድጋፎች ያስፈልጋሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ÷ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ሂደት ውስጥ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ አሰራርን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡

ለተፈናቀሉ ወገኖችችን ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ድጋፉ በመንግሥት አሠራር ውስጥ በአንድ ቋት የሚሰበሰብ መሆኑን ተገንዝቦ ፤ በዚህ አግባብ ብቻ መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማውደሙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወገኖች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ አውስተው፥ እስካሁን እነዚህን ወገኖች ለመርዳት የተንቀሳቀሰ አንድም አለማቀፋዊ የሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊ ተቋም እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡

በጠላት ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች በምግብ እና በመድኃኒት ችግር የሰው ሕይወት ማለፉንም ኮሚሽኑን ጠቅሶ አሚኮ ዘግቧል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version