Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ እና የሀረሪ ክልሎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ እና የሀረሪ ክልሎች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ አደረጉ ፡፡

የደቡብ ክልል ለመከላከያ ሰራዊት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ ሲያደርግ ÷ ድጋፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የመከላከያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት አስረክበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት ጥንት ኢትዮጵያውያን አባቶች መስዋዕትነት በመክፈል ነጻነቷ የተጠበቀ አገር ማቆየታቸውን አስታውሰው ÷ ኢትዮጵያውያን ለአገር ህልውና እና ነጻነት ዘብ ለቆመው የመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ደጀንነት በተግባር እያሳዩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ክልሉ ዛሬ ያደረገውን ድጋፍ ጨምሮ እስካሁን ከ830 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

የመከላከያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ተገኝ ለታ በበኩላቸው፥ የኀብረተሰቡ የደጀንነት ተግባር ሰራዊቱ ግዳጁን በድል እንዲወጣ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ጠቁመው ÷ ለሰራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ የሀረሪ ክልል ምስራቅ ዕዝ ሆስፒታል ግምታዊ ዋጋቸው 1 ሚሊየን ብር ለሰራዊቱ የዓይነት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ÷ ድጋፉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ለምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል አዛዥ ኮለኔል ብራሀነ ዘውዴ ነው ያስረከቡት፡፡

ርዕሰ መስተዳደሯ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ÷ የሀረሪ ክልል በአራት ዙሮች 80 ሚሊየን ብር ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው ÷ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍም ÷ ፍየሎች፣ በሶና የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው፡፡

በምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሆስፒታል አዛዥ ኮለኔል ብራሲል ዘዉዴ በበኩላቸው ÷ በጎ ፈቃደኛ ዘማች የህክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ እየሰጡት ከሚገኙት ሙያዊ እገዛ ባሻገር 22 ጉዳት የደረሰባቸውና ከፍተኛ ወጪ ይጠይቁ የነበሩ ጉዳቶች በክልሉ ሆስፒታሎች በነፃ መታከማቸውን ገልጸዋል፡፡

በምንያህል መለሰ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version