አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ትምህርትና ፖለቲካ መለያየት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በመድረኩ የትምህርት ጥራትን በአምስት ዓመታት ውስጥ የተሻለ ለማድረግ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የተመከረ ሲሆን፥ ከመምህራን ደምወዝና ጥቅማጥቅም፣ ከትምህርት ፖሊሲና ትምህርት ተቋማት መሪዎች አቅም ጋር በተያያዘ አገራዊ ጉዳዮች ተነስተው ተመክሮባቸዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገራዊ እና አህጉራዊ ችግሮች ላይ ምላሽ የሚሰጡ ምርምሮችን በመስራትና ምሁራንን በማፍራት እየተጋ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በትምህርት ዘርፉ እየታዩ ያሉ ችግሮች ለአገራዊ ችግር መንስኤ መሆኑ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፥ ከችግሩ ለመውጣት ምን መደረግ እንዳለበት እና ሁሉም የትምህርት ተቋማት በየደረጃው ከገቡበት ችግር እንዲወጡ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል የመምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ሃገራዊ ምክክርና የፖሊሲ ማሻሻያ የግብዓት ሃሳቦችን በመለገስ ረገድ ትኩረት እንደሚሰጠው በመግለጽ የመምህራን ጥቅማጥቅምንና ተያያዥ ጉዳዮችን ማስተካከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚመክሩበት ተናግረዋል፡፡
በምክክሩ የትምህርት ሚኒስትሩን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኢታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

