አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ጠላትን እንዲያጠፉና ሀገርን በዘላቂነት እንዲያስከብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡
የአማራ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን የተሰነዘሩ ሦስት የወረራ ሙከራዎችን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ፈንታሁን አየለ (ዶ.ር) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግንባታን በተመለከተ ባቀረቡት ጽሑፍ አብራርተዋል፡፡
ወታደር ሆነው ሀገራቸውን የመሩ በርካቶችን በማንሳት የውትድርና የሙያ ክብርንም ጠቅሰዋል፡፡
ከተሳታፊ ወጣቶች መካከል ኃይለኢየሱስ አለኸኝ÷ የተጋረጠብንን አደጋ ለመቀልበስ ወጣቶች በመሪዎቹ የሚሰጡ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ አለብን ብሏል፡፡
ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳር ዞን የውይይቱ ተሳታፊ በሪሁን ተፈራ በበኩሉ፥ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከፍተኛ አደጋ በተጋረጠባት በዚህ ወቅት አንድ ሆነን በመደማመጥ ችግሩን የምንቀለብስበት ጊዜ አሁን ነው ብሏል፡፡
በርካታ ግንባሮች ያሉ ቢሆንም ለመዝመት ዝግጁ ሆኜ እየተጠባበኩ እገኛለሁ ነው ያለው ወጣት በሪሁን፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል ከክብሮች ሁሉ ክብር መሆኑንም ገልጿል፡፡
“ጠላትህ ጠላት ብሎ ፈርጆ ሲመጣ አንተም ጠላትህን ለመመከትና አጸፋ ለመስጠት መዘጋጀት አስፈላጊ ነው” ሲሉ የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ወጣቶች አሸባሪው የህወሓት ቡድን አማራን ጠላት ብሎ የፈረጀ መሆኑን ተረድተው ጠላትን ለማሸነፍና ሀገርን በዘላቂነት ለማስቀጠል መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል አለባቸው ነው ያሉት፡፡
አሁን ባለው የህልውና ዘመቻ ጠላትን በተግባር መፋለም ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ÷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጠላትን መመከት የሚቻለው በጠንካራ የመከላከያ ኃይል እንደሆነ የገለጹት አቶ ገዱ÷ የአማራ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ጠላትን እንዲያጠፉና ሀገርን በዘላቂነት እንዲያስከብሩ ጥሪ አቅርበዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

