Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሽብር ቡድኑ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መዝረፍና ማውደሙ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት እና የህክምና መሣሪያዎችን መዘረፉንና ማውደሙን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በአማራ ክልል ከሚገኙ ሦስት ግዙፍ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ቅርንጫፎች መካከል የደሴ ቅርንጫፍ እጅግ ዘመናዊ እንደነበር የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እሸቴ ሹሜ እንደገለጹት÷ የደሴ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በምሥራቅ አማራ ለሚገኙ 60 ወረዳዎች፣ 29 ሆስፒታሎች፣ 308 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ከ45 በላይ የግል ጤና ተቋማት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ÷ ይህ ግዙፍ የመድኃኒት አቅራቢ ቅርንጫፍ ሙሉ በሙሉ በሽብር ቡድኑ ተዘርፏል፤ ወድሟል።

ከ70 በላይ በሲስተም የተያያዙ ኮምፒውተሮችም በሙሉ ተወስደዋል።

በቁጥር ከ80 እስከ 100 ሚሊየን የሚደርሱ የሕፃናት ክትባቶች የተዘረፉ ሲሆን ÷ ይህም በክልሉ የሚገኙ ሕፃናት ተገቢ የክትባት አገልግሎት እንዳያገኙ አሸባሪው ቡድን ባሰማራቸው ባለሙያዎች ሆን ተብሎ የተዘረፉ እና የወደሙ መሆኑን ነው አቶ እሸቴ ያመለከቱት ።

በኤጀንሲው ላይ ውድመት እና ዘረፋ ከተፈጸመ በኋላም የቀሩት መድኃኒቶችም በተከታታይነት ለህሙማን የሚሰጡ በመሆናቸው የሽብር ቡድኑ ወደ ውጭ አውጥቶ በመበታተን ከጥቅም ውጭ አድርጓቸዋል ነው ያሉት አቶ እሸቴ።

አሸባሪው የትህነግ ወራሪ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎችን መዝረፉንና ማውደሙን አቶ እሸቴ አረጋግጠዋል።

የኤጀንሲው ውድመት እና ዘረፋም በምሥራቅ አማራ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነውን ሕዝብ ለመጉዳት ታቅዶ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው ÷ መንግሥት እና ሕዝቡም በወራሪው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version