አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በበጋ ወራት ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ እንደገለጹት÷ በዞኑ የአገር ህልውናን ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት በተጓዳኝ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በዘንድሮ በጋ ወራት በ15 ቆላማ ወረዳዎች ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት 3 ሺህ ሄክታር ማሳ ታርሶ በዘር መሸፈኑን ነው ሃላፊው የገለጹት።
በልማቱ 38 ሺህ አባወራ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፥ ከልማቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግሉ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች መሰራጨታቸውን አብራርተዋል።
የባቢሌ ወረዳ የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አብዱሰላም መሐመድ በበኩላቸው÷ በግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና የልማት ሠራተኛች ንቅናቄ በመፍጠር የልማት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በወረዳው በዘንድሮ በጋ ወራት 1 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 200 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ነው የጠቆሙት፡፡
የባቢሌ ወረዳ ግብርና ባለሙያ አቶ ጌዲዮን ዓለማየሁ በወረዳው በበጋ መስኖ ከሚለማው 200 ሄክታር መሬት እስካሁን 100 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች በቡድኖች ተደራጅተው በልማቱ ሥራ እየተሳተፉ መሆናቸውንና የምርት ግብዓቶችም በወቅቱ እንደደረሱ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!