Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ‘ሰላም ፣ጸጥታና ልማት ትስስር በአፍሪካ’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ስብሰባ በበይነ መረብ ተካሄደ፡፡

ስብሰባው የህብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የኔፓድ እና የተመድ የአፍሪካ ተወካዮች በአስረጅነት የተሳተፉበት ውይይት በምክር ቤቱ የወሩ ሊቀ መንበር በኢትዮጵያ መሪነት ተካሂዷል፡፡

በወቅቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሰላም፣ ጸጥታ እና ልማት የአህጉሪቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሽብርተኝነት፣ መፈንቅለ መንግስት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል የፀጥታ ስጋቶች በመሆናቸው፥ የአህጉሪቱ የልማት ፕሮጀክቶች እና ፕሮግራሞች ተግባራዊ እንዳይሆኑ እና የተገኙ ስኬቶችም ወደ ኋላ እየተጎተቱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ አህጉሪቱን የሚገጥማትን የፀጥታ ተግዳሮት ለመግታት የመልማትን መብት በማክበር ወጣቶች እና ሴቶችን ማዕከል ያደረገ አካታች የልማት ፖሊሲዎችን መከተል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በንግግራቸው፥ የአፍሪካ የልማት መብቶች ከሌሎች የሲቪል መብቶች ጋር ጎን ለጎን እንዲራመዱ አባል አገራቱ በአንድ ድምጽ መናገር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አያይዘውም ወደ ፊት በአፍሪካ ሰላም፣ ፀጥታ እና ልማት ትስስርን በሚመለከት የሚካሄዱ ድርድሮች እንዲሁም የግጭት አፈታት እና ግጭቶቹ እንዳይከሰቱ መከላከል አስመልከተው የአፍሪካን ትርክትና ባህላዊ እሴቶችን ከግምት እንዲያስገቡ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ፥ መንግስት የሰብዓዊ መብት ማጣራት እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራው ካለው እንቅስቃሴ በተቃራኒ በተወሰኑ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አገራት አማካይነት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ ውድቅ እንዲደረግ የአፍሪካ አባል አገራት እና ወዳጅ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version