Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በበጋ ስንዴ ልማት ከ154 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረትና በምርት እንደሀገር ራስን ለመቻል ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ስንዴን በስፋት ለማምረት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር መለስ መኮንን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ በክላስተር ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በእርዳታ ሰበብ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በመከነ ስንዴ ለመፈፀም ጥረት ማድረጋቸው በምርት ራሳችንን ካለመቻላን የመነጨ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ይህን ከንቱ እቅድ ውድቅ ለማድረግ ስንዴን በመስኖ እያለማን ነው ብለዋል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ሀይል እና እርሱ የሚጋልባቸው የጥፋት ሀይሎች በከፈቱት ጦርነት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር መንግስት የመስኖ አቅም ባላቸው ክልሎች ስራውን በትኩረት እየመራ ይገኛልም ነው ያሉት።

በግብርናው ዘርፍ እንደ ሀገር 400 ሺህ ሄክታር መሬትን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን በእስካሁኑ ሂደት ከ154 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል በመስኖ በዘር እንደተሸፈነ ተገልጿል።

የመስኖ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በግብዓት፣ በዘመናዊ ማሽኖችና በሜካናይዜሽን በማገዝ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ሁሉም ለተጣለው ዕቅድ መሳካት በቁጭት መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ለመስኖ ስራ የሚውል የውሃ ሀብት ቢኖርም በተገቢው መንገድ በዘርፉ የሚገኘውን ምርት ማሳካት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ 13 ሺህ ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ የለማ መሆኑን የተናገሩት ሀላፊው ወራሪው የትግራይ ሀይል በክልሉ በምርት ላይ ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ኪሳራ ለማካካስ 80 ሺህ ሄክታር መሬትን በስንዴ ለማልማት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በቆላ ስንዴ የመስኖ ማልማት ስራ በክልሉ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፥ በጦርነቱ ምክንያት የርሃብ አደጋ ያንዣበበትን 6 ነጥብ 3 ህዝብ ለመመገብ ስንዴን በስፋት ማልማት ከሁሉ ተግባር ቀድሞ እየተሰራበት ነው ተብሏል።

አርሶ አደሩ የስራ ባህሉን በማሻሻልና የምርት ብክነትን በመቀነስ በጦርነቱ ምክንያት የታጣውን ሰብል መስኖን በመጠቀም ስንዴን በስፋት እንዲያለማ ጥሪ ቀርቧል።

በምናለ አየነው

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version