አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚደረገውን አሉታዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቃወም በፊንላንድ ሔልስንኪ ከተማ የ”በቃ” ንቅናቄ አካል የሆነ ሰልፍ ተካሄደ።
በሰልፉ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል፡፡
ሰልፉ መነሻውን ከፊንላንድ ፓርላማ ፊት ለፊት ያደረገ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ እና የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካባቢዎችን ያካለለ መሆኑን በጀርመን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአንዳንድ ሀገራት በኩል በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ሚዛናዊና ፍትሐዊ ያልሆነ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ላይም ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
የምዕራባውያን የዜና አውታሮች በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጩ ያለውን ሀሰተኛ ዘገባ እንዲያቆሙ የሚጠይቁ መፈክሮችም ተሰምተዋል፡፡
በተጨማሪም ሰልፈኞቹ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ጭፍጨፋ እና የንብረት ውድመት አውግዘዋል ።
በተመሳሳይ በደቡብ ሱዳን ጁባ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ኮሚዩኒቲ አባላት የተሳተፉበት የ”በቃ” ንቅናቄ አካል የሆነ ሠላማዊ ሰልፍ ተካሄዷል።
በሰልፉ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ባወጡት የአቋም መግለጫ አንዳንድ ሀገራት ለአሸባሪው የህወሃት ቡድን የሚሰጡትን የአይነትና የሞራል ድጋፍ በመጥቀስ ተቃውመዋል፡፡
በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ጐን መቆማቸውን በማረጋገጥ የሚደረግበትን ያልተገባ ዓለም አቀፍ ጫናና ጣልቃ ገብነትንም አውግዘዋል።
የምዕራባውያን የሚዲያ አውታሮች በአሸባሪው በህወሃት ቡድን የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በዝምታ በማለፋቸው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱም በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈራረሱ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባትና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል 20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለሶስተኛ ጊዜ ማሰባሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

