አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ኮሎራዶና ሲያትል እንዲሁም በስዊዘርላንድ ጄኔቭና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ወደ ሀገር ቤት ጉዞን አስመልክቶና የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሄዱ፡፡
በኮሎራዶና ሲያትል መድረኮች ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ፥ ኢትዮጵያ በህልውና ዘመቻ ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ዳያስፖራው እያከናወነ ባለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት የሀገር ባለውለታነቱንና አለኝታነቱን ማሳየት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ዳያስፖራው እያከናወናቸው ያሉ እነዚህ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
ዳያስፖራው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ እያደረገ ካለው ድጋፍ ጎን ለጎን እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በጄኔቫው መድረክ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዲሁም የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገንበቶ ተገኝተዋል፡፡
ዳያስፖራው ከታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጋር በተያያዘ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርገውን የህክምና ግብአቶች ድጋፍ ማቀላጠፍ ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ከጉዞ ጋር በተያያዘ ስለተሻሻለው መመሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሶስቱ መድረኮቹ ላይ የተሳተፉ የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮችና አባላት÷ ኢትዮጵያ ያለችበትን ይህን ከባድ ጊዜ እንድታልፍ የሁሉም ልጆቿን ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ ከሀገራቸው ጎን ለመቆም ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

