አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተገኘ ያለው ድል ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን ወደፊትም አንድ ሆነው በአሸናፊነት መቀልበስ እንደሚችሉ ሕያው ማሳያ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው ቡድን የፈጸመው ወረራ የአማራ ሕዝብ ለዓመታት ያፈራውን ሀብት በመዝረፍ፣ ተቋማቱን በማውደም፣ በማፈራረስ እና ሕዝቡን በመጨፍጨፍ አንገት ለማስደፋት እንዲሁም የኢትዮጵያዊነትን መሠረት ለመናድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የአሸባሪው የህወሃት ወራሪ የወንበዴዎች ቡድን እንዲሁም በሚደግፏቸው የውጪ ጠላቶች በአማራ፣ አፋር እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጦርነት ቢከፍቱም አሸናፊነትን በትውልድ ቅብብሎሽ ይዘው የተጓዙት ኢትዮጵያውያን ዛሬም አሸናፊ ሆነዋል ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡
ዶክተር ይልቃል “ኢትዮጵያውያን ሌላን ሀገር ለመውረር የተሰለፉበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፤ ገፍቶ ለመጣ ግን ምሕረት የላቸውም፤ በታሪካቸው የተሸነፉበት የጦር ግንባር ውሎ የለም” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድም መስዋእትነት በመክፈል የሀገሩን ሕልውና፣ ክብር እና ሕልውናን በማስጠበቅ የማይደፈሩ መሆናቸውን በድጋሜ አስመስክረዋል ብለዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያውያን ወደፊትም አንድነታቸውን አጠናክረው በሀገራቸው ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በአሸናፊነት መቀልበስ የሚችሉበት ሕያው ማሳያ እንደሆነ ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መላው ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው በመቆም በአዲስ መንፈስ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክት ማስተላፋቸዉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

